Tuesday, February 2, 2016

አንዳርጋቸው በምናቤ

ከተስፋዬ ገብረአብ

እነሆ! ቅዳሜ ዞሮ መጣ። በዚህች የቅዳሜ ምሽት ስለ አንዳርጋቸው ጥቂት አወጋ ዘንድ መንፈሴ መራኝ። አዲስ ነገር አትጠብቁ። ከቀንዱም ከሸኾናውም ዝም ብዬ አወጋለሁ። የምትሰሩት ሌላ አስቸኳይ ጉዳይ ካላችሁ ይህን ፅሁፍ ለማንበብ ጊዜአችሁን አታቃጥሉ። እንደው ዘና ብላችሁ ከሆነ ግን ብታነቡት ምንም አይላችሁም።
         አንዳርጋቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅሁት በደርግ ውድቀት ማግስት አዲስአበባ ላይ ሲሆን፣ እለቱ ቅዳሜ እኩለ ቀን ነበር። በዚያን ጊዜ አበበ ባልቻ እና ባለቤቱ መአዛ ብሩ ጓደኞቻቸውን አልፎ አልፎ ቅዳሜ ከመኖሪያ ቤታቸው ይጋብዙ ነበር። ማለትም ምሳ እንበላለን፤ ውስኪና ቢራም ይኖራል። ስነጥበብ እና ፖለቲካ እየቀላቀልን እናወጋለን። አማረ አረጋዊና መአዛ ብሩ የልጅነት የትምህርት ቤት ጓደኛሞች ነበሩ። እንግዲህ እኔም የዚህ የቅዳሜ ማህበር አባል የሆንኩት በአማረ በኩል ነበር። ካልተሳሳትኩ ስለዚህ ጉዳይ ከዚህ ቀደም በጨረፍታ የፃፍኩ ይመስለኛል።
አንዳርጋቸው ወደዚያች የቅዳሜ ማህበር መምጣት ጀመረ። ቀጭን ነበር። ትዝ ይለኛል እንደዛሬው ሰከን ያለ አልነበረም። ስሜታዊነት ይታይበት ነበር። ፀጉሩ ጥቁር ነበር። ጢም አልነበረውም። መንፈሱም ቁመናውም የጎረምሳ ነበር። ከቅዳሜ ማህበሩ አባላት መካከል ነቢይ መኮንን፣ እሸቱ ጥሩነህ፣ ተፈሪ አለሙ፣ ማንያዘዋል እንደሻው፣ ፍቃዱ ተክለማርያም እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ተድላ (?) የሚባል መንዜም በመካከላችን ነበር። ቀዌ ነገር ነው። ግጥም፣ ሙዚቃ ምናምን አይወድም። እያሽሙዋጠጠ ይሄን ፖለቲካ በጭንቅላቱ ያስኬደዋል።
ቃል በቃል ባይሆንም አንድ ቀን አማረን እንዲህ አለው።
“የኢትዮጵያ ስልጣኔና ስልጣን የትግሬ እና የአማራ መሆኑን አምናለሁ። እንግዲህ አሁን ለመግዛት ተራችሁ ሆኖአል። ያው አሸንፋችሁዋል መቸስ። እስክትሸነፉ ደግሞ ትገዛላችሁ። አንድ ነገር ግን በጥብቅ ማወቅ አለባችሁ። የምትወድቁበት ዘመን ሲደርስ ስልጣኑን መልሳችሁ ለኛ መተው ነው። OLF በመካከሉ ከገባ እናንተም እኛም የምንሊክን ቤተመንግስት  ለዘልአለሙ አናገኘውም። … ቆይ አታቋርጠኝ …. የለም! የለም! ስማኝማ … ብሄር ብሄረሰብ … እሱን እርሳው! ምንድነው የምታወራው?”
ተድላን በቁምነገር የሚሰማው አልነበረም። የማህበሩ ማጣፈጫ ነበር። አማረ አረጋዊ በወቅቱ የቴሌቪዥን መምሪያ ሃላፊ እንደመሆኑ፣ “ሰዎች ምን ይላሉ?” የሚል ተወዳጅ ፕሮግራም ጀምሮ ነበር። አንዳንድ ጊዜ እዚያ የምናወጋት ወግ ተፅፋና ተከሽና በፕሮግራሙ ላይ ትቀርባለች። አማረ ደጋግሞ ተድላን፣ “እዚህ የምትናገረውን ፃፈውና በቴሌቪዥን ይቅረብ” ይለዋል። አንድ ጊዜ በቁምነገር እንዲህ ሲናገረው ተድላ ሳቀ። ድምፁን ቀንሶም እንዲህ አለው፣
“ይሄ እኮ የቤተሰብ ጨዋታ ነው።” ከዚያም የአማረን ትከሻ ይዞ ሊያግባባው ሞከረ፣ “…የትግሬ ህዝብ ወንድማችን ነው። እየተፈራረቅን ገዝተናል፤ አይደለም እንዴ? ‘የሞትንም እኛ - የነገስንም እኛ’ እንዲሉ። የናንተ ችግር መቶ አመታት በተራራ መሃል ተቀብራችሁ መኖራችሁ ነው። አሁን ባነናችሁ። ‘ምኒልክ ዮሃንስን ሸውዶ ነው ዙፋን የያዘው’ ምናምን ብላችሁ እየተቆጣችሁ ስለመጣችሁ እንግዲህ ቤተመንግስቱንም ባንኩንም ትተንላችሁዋል። ርግጥ ነው፤ በአድዋ ጦርነት ከምኒልክ ጋር የመጣን ጊዜ አንዳንድ ጉዳት አድርሰናል። ብዙ ዛፎች ቆርጠናል። ብዙ ዶሮዎች ፈጅተናል። መቸም ይሄ በክፋት የተደረገ አይደለም። ካሳ ባለመደረጉ ብትቀየሙ እንገነዘባለን። ዋናው ነገር አሁን ረጋ በሉና አስቡ። መለስ ዜናዊን ታገኘዋለህ አይደለም? በግልፅ ንገረው። ሸዋን ስትለምዱ ጨዋታው ይገባችሁዋል። … ህዝብ … ህዝብ የምትሉትን ብትቀንሱ ይሻላችሁዋል። እውነት አይደለም። ህዝብ የሚባል ነገር የለም። ህዝብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ልንገርህ? ስለራሱ ብቻ የሚያስብ የግለሰቦች ጥርቅም ነው። ….መስሏችሁ ነው… እስክትለምዱት ነው። ገበሬ … አርሶአደር … እሱን ተወው!…ስማኝ ልንገርህ! …ገበሬ ማለት አቃጣሪ ማለት ነው።”
ፍቃዱ ተክለማርያም ክራር አንስቶ ማዜም ሲጀምር ከተድላ ሽሙጥና ፍልስፍና አረፍ እንላለን። ሰአሊው እሸቱ ጥሩነህ አንድ አሪፍ ግጥም ሲያነብ መንፈሳችን በቅኔ ውቅያኖስ ላይ ይንሳፈፋል። ነቢይ መኮንንም እጁን ወደ ኪሱ ሰዶ አንድ ቅጠል ወረቀት መምዘዙ የማይቀር ነበር። ጥቂት ወርቃማ ስንኞች አያጣም። የእሸቱ የስነ ግጥም ፍቅር ልክ እንደ መአዛ ብሩ ነው። ያበዱ ናቸው። እና ታዲያ ይህን የመሰለውን ውብ የቅዳሜ ማህበር ያፈረሰው አንዳርጋቸው ፅጌ ነበር። “ውስኪ እየጠጡ ግጥም ማንበብ፤ ዝባዝንኬ መስማት አልፈልግም!” ብሎ በሚቀጥለው ቅዳሜ እንደማይመጣ አሳወቀ። የፅጌ ልጅ ማህበራችንን ሲንቅብን እኛም ቀስ በቀስ ተውነው።
ከዚያ ወዲያ አንዳርጋቸው ቀልቤን የሳበው፣ “አማራ ከየት ወዴት?” በሚል ርእስ መፅሃፍ ፅፎ ሲያሳትም ነበር። ወዲያው መፅሃፉን ገዝቼ አነበብኩት። አንብቤ ስጨርስ በጣም ገረመኝ። አንዳርጋቸው ለመለስ ዜናዊ የቅርብ ሰው እንደነበር ይሰማ ነበር።  የጓደኝነታቸው መነሻ የአላማ አንድነት ነው ብዬ አምን ነበር። የተፈራ ዋልዋ ሚስት የአንዳርጋቸው እህት ናት። በመሆኑም አንዳርጋቸው ከአላማ አንድነት በተጨማሪ በጋብቻም ከኢህዴን (ብአዴን) ጋር በጥብቅ መተሳሰሩ ይሰማኝ ነበር። ከወያኔ ስርአት ጋር ተጣብቀው ሊቆዩ ከሚችሉ ባለስልጣናት ዋናው አንዳርጋቸው ነው የሚል እምነት ነበረኝ። “አማራ ከየት ወዴት?” የሚለውን መፅሃፍ ሳነብ ግን አንዳርጋቸውን በትክክል አወቅሁት። በጠባዩ ነፃ እና አፈንጋጭ መሆኑን ተረዳሁ። ብዙም አልቆየ። ወያኔን አውግዞ እንደገና ወደ እንግሊዝ አገር ተሰደደ። ከዚያም ለረጅም ጊዜ ድምፁ ሳይሰማ ቆየ።
በመቀጠል ስለአንዳርጋቸው የሰማሁት በምርጫ 97 ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ነበር። ብዙም አልቆየ የቅንጅት አመራር ከመታሰሩ በፊት ወያኔ አንዳርጋቸውን በፖሊስ  ይዛ እየደበደበች ዝዋይ አሰረችው። የቅንጅት አመራር ሊታሰር ጥቂት ሲቀረው ደ’ሞ አንዳርጋቸው ከእስር ተፈትቶ ወደ ለንደን ተመልሶ ኮበለለ። ግንቦት 7ን እስኪመሰርት ድረስም በስደት ላይ ሆኖ የተቃዋሚውን ትግል በመምራት ግንባር ቀደም ነበር።
አንድ ጊዜ ለአንድ ወር እረፍት ከሆላንድ ወደ ኤርትራ ሄጄ ሳለ አንዳርጋቸው አስመራ መኖሩን ሰማሁ። ላገኘው መጓጓቴ ትዝ ይለኛል። እሱም አስመራ መሄዴን ሰምቶ ኖሮ ቀድሞ ስልኬን አገኘና ደወለልኝ። ኤክስፖ ሆቴል ተቀጣጠርን። ሳገኘው በአካል ብዙ ተለውጦ አገኘሁት። ጠጉሩ ገብስማ ሆኖአል። ጥቂት ክብደት ጨምሮአል። ንግግሩ ግን አልተለወጠም ነበር። እንደቀድሞው ፊት ለፊት ይናገራል። ጉራ የለበትም። ሰዎችን በቀላሉ ጓደኛው የማድረግ ችሎታውም አብሮት ነበር።
ያን ቀን እስከ እኩለ ሌሊት ቆየን። በብዛት እሱ ነበር የሚናገረው። የማልስማማባቸው የፖለቲካ አመለካከት ቢኖሩትም የፅጌ ልጅ የስልጣን ጉጉት እንደሌለው መረዳት ችዬ ነበር። “ለሚቀጥለው ትውልድ ምንድነው የምንተውለት? ቅርሳችን፣ ባህላችን፣ ታሪካችን…” እያለ በምሬትና በቁጭት ይናገር ነበር። ከዚያ በሁዋላ ከአንዳርጋቸው ጋር በአስመራ እና በአምስተርዳም በተደጋጋሚ ተገናኝተናል። በወያኔ ተጠልፎ እስኪወሰድ ድረስም መልካም ግንኙነት ነበረን።
ጊዜ ሰውን ቆሞ አይጠብቅም። የአምስት ኪሎ ባለቅኔ “መንገዱ ፈጣን ነው - የሰው ህይወት ጉዞ፤ ይጋልባል እንጂ - ቆሞ አያይም ፈዞ” እንደሚለው ነው። አንዳርጋቸው በወያኔ ሲጠለፍ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ሊፈረስ እንደሚችል ገምቼ ነበር። ወያኔም እንዲሁ ነበር ያሰበው። አንዳርጋቸውም ቢሆን ከታሰረበት ቦታ ሆኖ ሲናገር እንደሰማነው የግንቦት 7 የትጥቅ ትግል የመቀጠል ተስፋ እንደሌለው ነበር የተነበየው። እሱን ተክቶ፣ በረሃ ወርዶ፣ ትግሉን የሚያስተባብር አመራር ማግኘት ስለመቻሉ ጥርጣሬ ነበረው። ብርሃኑ አንዳርጋቸውን ተክቶ በረሃ ይገባል ተብሎ የሚታሰብ አልነበረም። ፕሮፌሶር ብሬ ሁዋላ አፋችንን አስያዘን እንጂ፤ በሃሜት ቦጫጭቀነው ነበር። ብርሃኑ አሜሪካ ላይ ከቤተሰቡ ጋር መኖሩ፤ የመምህርነት ቋሚ ስራ መጀመሩ፤ አንዳርጋቸውም ተስፋ የቆረጠ መስሎ መታየቱ ተደማምሮ ብርሃኑን እንድናማው አደፋፍሮን የነበረ ይመስለኛል።
በዚህም ተባለ በዚያ የአንዳርጋቸው መጠለፍ የግንቦት ሰባትን ትግል አጠናከረው እንጂ አላዳከመውም። ከዚህ አንፃር ወያኔ ከስራለች። አሳምራ ተሸውዳለች። አሁንም ቢሆን ለወያኔ የሚሻላቸው አንዳርጋቸውን በሚቀጥለው አውሮፕላን ወደ ለንደን መላክ ነው። ምክንያቱም አንዳርጋቸው ለታጋዮች የብርታት ሻማ ሆኖ እያገለገለ ነው። ትግሉን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ የሚጎርፉት ወጣቶች አንዳርጋቸውን በአእምሮአቸው መያዛቸው እውነት ነው። አንዳርጋቸው የነገ የአመፅ መነሻም ሊሆን ይችላል። ስብሃት ነጋ ይህችን በጎ ምክር እንደሚያጤናት ተስፋ አደርጋለሁ።
ብርሃኑ ነጋን አጊንቼው አላውቅም። በአጋጣሚ ያዩት ሰዎች ይነግሩኛል። አንድ ጊዜ ግን (ከ60 ቀናት በፊት) ቀይባህር ዳርቻ መንገዶች በጎርፍ ተዘግተውበት ብርሃኑ ሌሊቱን በረሃ ላይ ማደሩን ሰምቻለሁ። እኔም በአካባቢው ነበርኩ። ከውጭ አገር ከመጣ እንግዳ ጋር ወደ አዱሊስ ከተማ እየተጓዝኩ ነበር…
በነገራችን ላይ የዘንድሮው የምፅዋ ክረምት በፍፁም ታይቶ የሚታወቅ አይነት አይደለም። ከህዳር መጨረሻ ጀምሮ እንደ ጉድ ይረግጠዋል። ምፅዋ ላይ ፀሃይ የለችም። ቀይባህር ቀዝቅዟል። ከባድ ማእበልም አለ። በዚህ አይነት የአየር ጠባይ መዋኘት ብዙም ደስ አይልም። የምፅዋ ነዋሪዎች ብርድ ልብስ ተከናንበው የመተኛት አጋጣሚ በማግኘታቸው ተገርመዋል። በቆሎና ማሽላ፣ እንዲሁም ቡልቱግ ጥሩ ይዘዋል። በርግጥ ዝናቡ ከመበርታቱ የተነሳ ጎርፉ ጥቂት የገበሬ ጎጆዎችን እንደ ዘንቢል አንጠልጥሎ ቀይባህር ጨምሯቸዋል። ሂርጊጎ ወይም ገልአሎ አካባቢ ስድስት ሰዎች በተኙበት በጎርፍ መወሰዳቸውም አቢይ ዜና ሆኖ ሰንብቶ ነበር።
… አሳባችን እንኳ ከእንግዳው ጋር ፎሮ ከተማ አድረን ስናበቃ በማለዳው ወደ አዱሊስ ለመሄድ ነበር። ሳይቻል ቀረ። እንዳልኩት ሃይለኛ ጎርፍ መንገዱን ዘግቶ ጠበቀን። ባለ ከባድ ማርሽ መኪና ይዘው ጎርፉን ለመሻገር የሚሞክሩ፤ የኤርትራን ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎችም አፋፉ ላይ ነበሩ። ብርሃኑ ነጋ ያለበት ቡድን በሁለት ጎርፎች መካከል መያዙን አንደኛው ወታደር ነገረኝ። እንዳጫወተኝ ከሆነ ይህ ጎርፍ መንገዱን ከመዝጋቱ በፊት ነበር እነ ብርሃኑ የተሻገሩት። ከፊታቸው ግን ሌላ አደገኛ ጎርፍ መንገድ ዘግቶ እንደ ፈረሰኛ እየተገላበጠ ወደ ቀይባህር ሲገባ ጠበቃቸው። እነ ብርሃኑ ወደፊት መቀጠል ስላልቻሉ ወደ ምፅዋ ለመመለስ ፊታቸውን አዞሩ። ከሁዋላቸውም ግን መንገዱ በአዲስ ደራሽ ፈረሰኛ ጎርፍ ተዘግቶ ጠበቃቸው። በመካከሉ የጎርፍ እስረኛ ሆኑ።
“ለእርዳታ እየሄዳችሁ ነው?” ስል ጠየቅሁት።
“ችግር እንዳይኖር ለማየት ነበር። ማለፍ አልቻልንም።”
“እነ ብርሃኑ ወዴት እየሄዱ ነበር?”
“እሱን አላውቅም።”
“ወደ አሰብ ነው ወይስ ወደ ዊኣ?”
“አላውቅም በእውነቱ” ብሎ ገልመጥ አደረገኝ።
“ስንት ናቸው?” ስል ጥያቄየን አራዘምኩ።
መልስ ሳይሰጠኝ ዝም በማለቱ፤ ጥያቄየን ማቆም እንዳለብኝ ተረዳሁ።
በዚያን ሌሊት ሴንትራል ሆቴል ነበር ያደርኩት። በረንዳው ላይ ቁጭ ብዬ የባህሩን የማእበል ድምፅ እየሰማሁ ነበር። ባህሩ ላይ በርቀት መብራት ይታያል። መርከብ መሆን አለበት። በፀጥታዬ ውስጥ ሳለሁ ታዲያ እግዚአብሄርን እንዲህ አልኩት፣
“ታታሪ ነጋዴ ወይም ብርቱ ግንበኛ ልታደርገኝ እየቻልክ፣ ያለእውቅናዬ ፀሃፊ ያደረግኸኝ አምላክ ሆይ! በል እስኪ የምር ፈጣሪ ከሆንክና ችሎታው ካለህ የምናቤን ሻማ ለኩስና አንዳርጋቸው ምን እያደረገ እንዳለ ገልጠህ አሳየኝ?”
ፈጣሪ በምናቤ በኩል መጣና፣ “አይንህን ጨፍን!” አለኝ። እንደታዘዝኩት አይኖቼን ጨፈንኩ። አይኖቼን ስጨፍናቸው የምናቤ መስኮቶች ተከፈቱ። አንዳርጋቸውንም አየሁት።
….ቀጭን አልጋ ላይ በጀርባው ጋደም ብሎ ነበር። ከግድግዳው ጥግ ላይ ቡኒ ጠረጴዛ ይታያል። አንዳርጋቸው ከአልጋው ብድግ ብሎ በር ከፍቶ ወጣ። ከትንሿ ደጃፍ ላይ አንዲት የእንጨት ወንበር አለች። ቁጭ አለ። ሰማዩን ቀና ብሎ አየው። እጁን አነሳና ጢሙን ሞዠቀ። ጢሙና ጠጉሩ ሃጫ በረዶ መስሎአል። ጥርሶቹ አይታዩም። እንደ አውሮፓውያን ስስ የሆኑት ከንፈሮቹ እንደ ኪዊ የቀለም ቆርቆሮ ግጥምጥም ብለው ተዘግተዋል። ቅንድቦቹ የጥርስ ቡሩሽ ይመስላሉ። ከተቀመጠበት ተነሳና ወደ እስር ክፍሉ ገባ። ጠረጴዛው ላይ ቁጭ ብሎ ኮምፕዩተር ከፈተ። ምንም አልፃፈም። ዘጋውና ተነሳ። ወደ ደጅ ወጣና በረንዳው ላይ ቁጭ አለ። ሰማዩ ላይ መልሶ አፈጠጠ። ከጥቂት ደቂቃዎች ማፍጠጥ በሁዋላ አይኖቹን ጨፈናቸው። በዚያ መልኩ ብዙ ቆየ። በመካከሉ የበር መከፈት ድምፅ ሰማ። አይኖቹን ግን አልከፈተም። ማን እንደመጣ ማየት አላስፈለገውም። የራት ሳህን የያዘ ፖሊስ ነበር። አንዳርጋቸው አይኖቹን ከፈተ። ፖሊሱ ሳህን እና ውሃ ካስቀመጠለት በሁዋላ ቁጭ አለ፣
“ምን አለ አዲስ ነገር?” ሲል ጠየቀው።
“ምንም የለም።”
“የኦሮሞዎች አመፅ እምን ደረሰ?”
“ቀጥሎአል። ብቻ እየቀዘቀዘ ነው የሚሉም አሉ።”
“የሞቱትስ ስንት ደረሱ?”
“ብዙ ነው! ከመቶ በላይ ይሆናል…”
“በሌላ አካባቢ አመፅ የለም?”
“ምንም የለም።”
“ስለ ብርሃኑስ ምን ወሬ አለ?”
“ምንም የለም። እዚያው ነው።”
ከጥቂት ዝምታ በሁዋላ ፖሊሱ ጠየቀው፣
“የምትፈልገው ነገር አለ?”
“ምንም የለም።”
“ትበሳጫለህ እንዴ?”
አንዳርጋቸው በስሱ ሳቀ፣
“አሳሪም ታሳሪም በቅርቡ ተያይዘን እናልፋለን። ታሪክ እና ትእዝብት ብቻ ይቀራሉ።” 

ከጥቂት ደቂቃዎች በሁዋላ ፖሊሱ ተሰናብቶ ወጣ። አንዳርጋቸው አይኖቹን ወደ ሰማይ ተከለ። ጨረቃዋን በሩቅ ርቀት አያት። የልጃገረዶች የፊት መመልከቻ መስታወት መስላ ሰማዩ ላይ ተለጥፋለች። እና አንዳርጋቸው እንደገና አይኖቹን ጨፈነ።     
 Gadaa Ghebreab  የቅዳሜ ማስታወሻ   ttgebreab@gmail.com    www.tgindex.blogspot.com   Jan. 30 2016                    

1 comment:

Anonymous said...

I do not have words to tell you how much I fall in love with your extraordinary quality of writing. Whenever I get your piece of article online, oh my goodness, reading does not express my feeling but I can say I indulge into the warmth of the literature and make euphoria of the chocolate.

But as individual and most importantly of Ethiopian, I am not always in agreement with your characterization and the narration of your article.

It is how the world works benevolence and malevolence.

Tesfaye