Saturday, September 28, 2013

“ላይፍ” መፅሄት - አዲስ አበባ - ቃለመጠይቅ


·         አዲሱየስደተኛው  ማስታወሻመጽሐፍህ የደራሲው  ማስታወሻእና የጋዜጠኛው  ማስታወሻ  በምን  ይለያል? 

Ø  የስደተኛው ማስታወሻ” ከቀዳሚዎቹ ማስታወሻዎች የቀጠለ ነው። በዚህ ቅፅ በተመሳሳይ ገጠመኞቼን ነው ያሰፈርኩት። በርግጥ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ የአውሮፓ የስደት ገጠመኞቼ ተተርከውበታል። ይህ ቅፅ የማስታወሻዎቼ መደምደሚያ ሲሆን፣ ከዚህ በሁዋላ ወደ ስነፅሁፍ ስራዎች ነው የምገባው። 

·         የስደተኛው ማስታወሻአሳታሚ ማነው? መቼ ለገበያ ይቀርባል? 

Ø  ነፃነት አሳታሚይባላል። ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኝ የኢትዮጵያውያን ንብረት የሆነ አሳታሚ ድርጅት ነው። ውል አድርገን መፅሃፉን አስረክቤያለሁ። የጀርባና የፊት ሽፋኑን ዲዛይን ሰርተው ልከውልኝ አፅድቄያለሁ። መፅሃፉ በህትመት ፕሮሰስ ላይ እንደሆነ መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ነግረውኛል። ጥቅምት ገበያ ላይ ይውል ይሆናል። በትክክል ቀኑን አላውቅም። መረጃዎቹን በድረገፃቸው በኩል ይፋ ያደርጉታል።


·         አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ስራዎችህ የሁለት ተለያዩ ሰዎች ተጽዕኖ ውጤት ነው ይላሉ፡፡ ከአሰፋ ጫቦ ሽሙጥን፣ ከበዓሉ ግርማ ጀብደኝነትን። ምን ትላለህ? 

Ø  አሰፋ ጫቦ አሽሟጣጭ ነው ብዬ አላስብም። በአሉ ግርማም ጀብደኛ አይመስለኝም። ስለሁለቱ ብእረኞች በዚህ መንገድ ማሰብ ስህተት ነው። የአሰፋ ጫቦን ብዕር አደንቃለሁ። አሽሟጣጭ ሳይሆን እውነታዎችን በቀጥታና በግልፅ የሚናገር ደፋር ብእረኛ ነው። በአሉም የሰከነ ብዕር የነበረው ደራሲ ነው። ጀብደኛ ሊያሰኘው የሚችለው ስራው የቱ ነው? ምናልባት “ኦሮማይ”ን በማሰብ ከሆነ፣ በአሉ ግርማ በዚህ መፅሃፍ ምክንያት ሊገደል እንደሚችል ቢገምት ኖሮ ከዚያ የተሻለ ስራ ይሰራ ነበር። ወደ ጥያቄው ስመለስ የበአሉና የአሰፋ ጫቦ ተፅእኖ የለብኝም ለማለት አልችልም። ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ግን የወርቃማው ዘመን የሩስያ ደራስያን ብእረኞች ይበልጥ ቀልቤን ይስቡታል። እንደምገምተው ማስታወሻዎቼ ይበልጥ የቱርጌኔቭ የህይወት ታሪክ ማስታወሻዎች ተፅእኖ ሳይኖርባቸው አይቀርም። ወደ ትረካው ጥበብ ስንመጣ ስብሃት ገብረእግዚአብሄርና ጎርኪይ ምንግዜም አብረውኝ አሉ። ዞረም ቀረ አንድ የብዕር ሰው በጊዜ ሂደት በተለያዩ ፀሃፊዎች የአፃፃፍ ስልት ሊገነባ ይችላል። 

·         በአሁን ጊዜ ለአማርኛ ስነ ጽሑፍ ምን ያህል ቅርብ ነህ? ከታተሙት መፃህፍት መካከል የምታደንቀው አ? ‘አብሬው በሰራሁ’  ስለምትለው ወይም በልዩ ሁኔታ ስለምታስታውሳቸው ደራስያን የምትገልፀው ካለም  እድሉን ልስጥህ? 

Ø  ለአማርኛ ስነፅሁፍ ቅርብ ነኝ ለማለት አልችልም። የሚታተሙ መፃህፍትን እንደልቤ ለማግኘት ስለምቸገር ስለታተሙ መፃህፍት በልበ ሙሉነት አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ። በጥቅሉ ግን የአማርኛ ስነፅሁፍ አደጋ ላይ የወደቀ ሆኖ ይሰማኛል። አማርኛ በአዲሳባና በአማራ ክልል ቋንቋነት ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ብዙ ተሰርቶበታል። ይህ ሁኔታ የአማርኛ ስነፅሁፍን ክፉኛ ጎድቶታል።  አማርኛ ቋንቋ ጠላት ስለበዛበት ስነፅሁፉም ባለቤት አጥቶአል። ይህ አሳዛኝ እውነት ነው። 

ስለ ደራስያን ወይም ስለ ብዕር ሰዎች የጠየቅኸኝ ጥያቄ ስሜታዊ የሚያደርግ ነው። በልጅነቴ ሳመልካቸው የኖርኩት አንዳንዶቹ የብዕር አማልክት ዛሬ በህይወት የሉም። ከጥቂቶቹ ጋር ከመተዋወቅ በላይ አብሬያቸው ለመስራት በቅቻለሁ። የቅርብ ጓደኞቼ የሆኑም አሉ። ከስብሃት ገብረእግዚአብሄር ጋር አብሬ በመስራቴ በምንም ነገር የማይለካ ልምድ አጊንቼያለሁ። የአርትኦትን ጥበብ ከአረፈአይኔ ሃጎስ ተምሬያለሁ። እሸቱ ተፈራ ቤተመፃህፍት ማለት ነበር። ማሞ ውድነህ ወዳጄ ነበሩ። “እነዚህ አለቆችህ” እያሉ ወያኔን ያሙልኝ ነበር። አበራ ለማ ወጣቶችን በማገዝ ሱስ የተለከፈ ደራሲ ነበር። የሺጥላ ኮከብ ምርጥ ደራሲ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ነካ ያደርገዋል። የእፎይታ መፅሄትን አንደኛ አመት ስናከብር መጣና እንዲህ አለኝ፣
“አንድ የማይረባ መፅሄት አንድ አመት ስለሞላው ምንድነው ይህ ሁሉ ቸበርቻቻ?”
የሺጥላ ይህን ሲናገር ነጋሶ ጊዳዳ እና አለምሰገድ ገብረአምላክ በአካባቢው ነበሩ።
“ሞቅ ስላለህ ወደ ቤትህ ሂድ” አልኩት። 
መአዛ ብሩና አበበ ባልቻ የልብ ወዳጆቼ ነበሩ። ሃይስኩል እያለሁ ከመአዛ ብሩ ድምፅና ሳቅ ጋር ፍቅር ይዞኝ ነበር። አሁንም አልተወኝም። የመአዛን ሳቅ ለመስማት ስል የሸገር ሬድዮ ቁራኛ ነኝ። ተፈሪ አለሙና ማንያዘዋል እንደሻውን አልረሳቸውም። የማንያዘዋል ወንድም ይሁን እንደሻው ራሱ አሪፍ ፀሃፊ ነው። ከሳህለስላሴ ብርሃነ ማርያም እና ከአያልነህ ሙላቱ ጋር ባለመስራቴ በጣም ይቆጨኛል። ከተሰደድኩ በሁዋላ ግን ለአያልነህ ደወልኩለት። የማክሲም ጎርኪይን የትውልድ ቦታ ኒዥኒይ ኖቭጎሮድን ለመጎብኘት ፈልጌ ስለነበር አስጎብኚ እንዲያዘጋጅልኝ ለመጠየቅ ነበር የደወልኩለት። ሃይለመለኮት መዋእል ከኔ ጀግኖች አንዱ ነው።
 በፍቃዱ ሞረዳን አልወደውም። ምክንያቱም ከመሬት ተነስቶ ነገር እየፈለገ ያበሳጨኛል። ተወኝ ብለው ሊተወኝ አልቻለም። 2009 ላይ ጦርነት ገጥመን ነበር። በቅርቡ ግን አሪፍ ግጥም ፅፎ ሳነብ ያናደደኝ ሁሉ ብን ብሎ ስለጠፋ አድናቆቴን በፅሁፍ ገለጥኩለት።
ምነው አብሬያቸው በሰራሁ የምላቸው በርካታ ወጣት የብእር ጀግኖች አሉ። በእውቀቱ ስዩም፣ ኑረዲን ኢሳ፣ ሲሳይ አጌና፣ ኤፍሬም ስዩም፣ አዳም ረታ፣ ይስማእከ ወርቁ፣ ማረፊያ በቀለ…እንዲህ እያልኩ ትዝታዬን ከቀጠልኩ መቶ ገፅ አይበቃኝም። ጥያቄህን መልሼልህ ይሆን?  

·         ለአንድ ጀማሪ ደራሲ በአንተ አስተውሎት መጠንና ጉልበት  እንዲጽፍ ምን ትመክረዋለህ? 

Ø  በርግጥ በአስተውሎትና በብርታት እየፃፍኩ መሆኔን ካመንክ አመሰግናለሁ። ተሰጥኦ ያለው ጀማሪ ደራሲ ጥሩ የሚባሉ መፃህፍትን በጥንቃቄ መርጦ በዝግታ ያነብ ዘንድ እመክረዋለሁ። ብዙ ማንበብ ብቻውን ጥሩ ደራሲ አያደርግም። መምረጥና በጥልቀት ማንበብ ይገባል። በጥልቀትና በዝግታ ማንበብ ሲባል ታሪኩን ብቻ አይደለም። ቃላት አመራረጥ፣ አረፍተነገር አሰካክ፣ የአገላለፅ ዘዴዎችን በጥንቃቄ መመርመር ማለት ነው። ሌላው ጉዳይ ጀማሪ ደራስያን ያልኖሩበትን ህይወት ለመፃፍ እንዳይሞክሩ እመክራለሁ። ልጅ ያልወለደ ሰው ስለ ልጅ ፍቅር ሊያውቅና ሊፅፍ አይችልም። ቢፅፍም የተሳካለት አይሆንም። ስለ ገበሬ መፃፍ ከፈለጉ ጥቂት ቀናትን ከገበሬዎች ጎጆ ማሳለፍ መቻል አለባቸው። ይህን ጉዳይ ቼኾቭ አጥብቆ መክሮ ነበር። ስሞክረው ልክ እንደሆነ አወቅሁ። “በብርታት መፃፍ” የሚለው መቸም አከራካሪ ነው። እኔ በብርታት እየሰራሁ ያለሁት (በርግጥ ከሆነ) ሙሉ ጊዜዬን በፅሁፍ ስራ ላይ ስላዋልኩ ሊሆን ይችላል። ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች ሌላ ምንም ስራ ሳይሰሩ ፅሁፍ ላይ ብቻ የሚያተኩሩበት እድል ካገኙ በብርታት ብዙ ሊሰሩ ይችሉ ይሆናል። ኑሮውን ለመደጎም ሲል የማይወደው ስራ ላይ የሚባክን የብዕር ሰው የተሳካለት ስራ ለመስራት ይቸገር ይሆናል።  

·         ፖለቲካ ውስጥ ባይገባ ኖሮስመጥር” ከሚባሉት ደራስያን መካከል  አንዱ ይሆን ነበር ለሚሉት ምን ምላሽ አለህ? 

Ø  በአንድ ወቅት የኢህአዴግ አባል የሆንኩት ከፍላጎቴና ከእውቅናዬ ውጭ መሆኑን ተናግሬያለሁ። ከወያኔ ጋር በቆየሁበት ጊዜም ቢሆን ጋዜጠኛ ሆኜ ነው የሰራሁት። ከዚያ በሁዋላ ነፃ ሰው ነኝ። የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም።  “ፖለቲካ ውስጥ ባይገባ” የሚለው አባባል የተጋነነ ነው። የኛ ዘመን ሰው እንዴት ከፖለቲካ መራቅ ይችላል? እንራቅህ ቢሉትስ መች ይሆናል? እንደ ጭስ ቀዳዳ ፈልጎ መኝታ ቤታችን ድረስ ይገባል። በአጋጣሚ ፖለቲካ ውስጥ ስለገባሁ እንደ ጋዜጠኛ እና እንደ ደራሲ የፖለቲካ ገጠመኞቼን ፅፌያለሁ። ይህን በማድረጌ ስህተቱ ምን ላይ እንደሆነ ሊገባኝ አይችልም። እርግጥ ነው፣ አምርረው የሚጠሉኝ ወገኖች አሉ። ከፖለቲካ አመለካከታቸው ተነስተው ሊሆን ይችላል።  የምሰራው ስራ ዋጋ ካለው ክብር ያገኛል ብዬ አስባለሁ። እኔ ማድረግ ያለብኝ ልቤን መከተል ብቻ ነው።  

·         የስደተኛው  ማስታወሻመጽሐፍህ  ገር ውስጥ እንዲነበብ ምን ጥረት ታደርጋለህ? 

Ø  ለአዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር መልእክት ልኬ ነበር። ምላሽ አላገኘሁም። አንድ የኮክቴል ግብዣ ላይ በወሬ መካከል ስብሃት ነጋ፣ ለበረከት “ለምን አትተወውም? ያሳትም” ብሎት እንደነበር ሰምቻለሁ። በርግጥ ከዚህ አባባል ተነስቼ ችግሩ ያለው በረከት ስምኦን ጋር ብቻ ነው ለማለት አልችልም። በዚያም ሆነ በዚህ ግን ከመነበብ ሊያግዱት አይችሉም። ኮፒው በህገወጥ መንገድ ታትሞ መሰራጨቱ አይቀርም። የስርአት ለውጥ ሲደረግ ግን የታገዱትን መፃህፍት በድጋሚ አሳትማቸዋለሁ። 

·         ኢሕአፓዎች ይሔንንም መጽሐፍህ እንደማያባዙት ምን ዋስትና አለህ? 

Ø  መሞከራቸው አይቀርም። የሚያሰራጩባቸው ድረገፆችና የፊስቡክ ክፍሎች ስለሚታወቁ ህገወጡን ድርጊት ከፈፀሙ በህግ እንዲጠየቁ ጠበቆችን አዘጋጅተናል። በ’ርግጥ ኮፒ የማድረጉን ስራ የሚሰሩት የኢህአፓ ሰዎች ብቻ ናቸው ማለት አይቻልም። የምቀኝነት ህመም ያለባቸው አንዳንድ የአእምሮ በሽተኞችም ድርጊቱን ሊፈፅሙት ይችላሉ። በርግጠኛነት የምነግርህ ወያኔዎች ይህን ድርጊት እንደማይፈፅሙት ነው። የማይፈልጉትን መልእክት በማፈን እንጂ በማሰራጨት አይታወቁም። የኢህአፓ አመራር የኮሎኔል መንግስቱን መፅሃፍ ስካን አድርጎ ሲያሰራጭ መንግስቱ ሃይለማርያምን ገንዘብ ማሳጣት ነበር አላማቸው። የሚያስቅ ጅልነት ነው።  መንግስቱ ገንዘብ አይፈልግም። ቀዳሚ አላማው መፅሃፉ እንዲነበብ ነው። ስለዚህ ኢህአፓ ማድረግ የነበረበት መፅሃፉን ገዝቶ ማቃጠል ነበር።  

·         ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ዕድሉ  ያለ ይመስልሃል?

Ø  የሕወሓት ስርአት ከወደቀ እመለሳለሁ። 

·         አዲስ አበባ ውስጥ የሚናፍቅህ የትኛው ቦታ ነው? ቁጭ ብለህ ቡና ወይም ቢራ ለመጠጣት የምትመርጠው ቦታስ? 

Ø  አዲስአበባ ብዙም አይናፍቀኝ። ይልቁን ደብረዘይት እና የስምጥ ሸለቆ ከተሞች ይናፍቁኛል።ጋራቦሩ ኮረብታ ላይ ቆሜ የረር ተራራን በሩቅ ማየት በጣም ይናፍቀኛል። ቢሾፍቱ ሃይቅ ዳርቻ ከሚገኙ መሸታ ቤቶች ተቀምጬ ማምሸት እፈልጋለሁ። የባቦጋያና የሆራ አርሰዲ ዳርቻዎች በህልሜ እንኳ ይታዩኛል። ድፍን አድአ፣ እስከ ጨፌ ዶንሳ፣ እስከ ሎሜ፣ ያደግሁበት አገር ነው። በቢሾፍቱ ገደሎች ደረት ላይ እንደ ወፍ በረናል። ጋራቦሩን ጋልበንበታል። በህይወት ዘመኔ አንድ ጊዜ ወደነዚህ የአድአ ገጠሮች መሄድ እፈልጋለሁ። ርግጥ ነው፣ የወያኔ ስርአት ሲወድቅ በሚቀጥለው አይሮፕላን ቦሌ ከሚያርፉት መንገደኞች አንዱ እኔ ነኝ። እና ሽው ወደ ቢሾፍቱ!  

·         በቡርቃ ዝምታ እና በቢሾፍቱ ቆሪጦች መጽሃፍትህ የተጸጸትክበት አጋጣሚ አለ? አሁንም ያለህ አቋም የመጽሐፍቱ ነጸብራቅ ነው? 

Ø  በመፃህፍቱ የምፀፀትበት ምክንያት የለም። ይህ ማለት ድክመት የለባቸውም ማለት አይደለም። በ20ዎቹ መጨረሻ እድሜ ላይ ሆኜ የፃፍኳቸው መፃህፍት እንደመሆናቸው ድክመት ሊኖርባቸው ይችላል። የህይወት ልምድ ማጣት፣ ሊንፀባረቅባቸው ይችላል። የቢሾፍቱ ቆሪጦች ከስነፅሁፍ አንፃር ሊተች የሚችል ነው። ድክመት አለበት። እንዲህ ያለ ነገር ሊያጋጥም ይችላል። በአሉ ግርማ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” ተበላሽቶበታል። ጥሩ አልነበረም። ብርሃኑ ዘርይሁን በወጣትነቱ የፃፋቸውን፣ “ጨረቃ ስትወጣ” አይነቶቹን ተመልሰህ ብታነብ ብርሃኑ ነው የፃፋቸው ለማለት ትቸገራለህ። ስነፅሁፋዊ ክህሎት እያደገ ስለሚሄድ በገፀባህርያት ቀረፃ ላይ ድክመት ሊታይ ይችላል። የሃያስያን መኖር አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው። የቡርቃ ዝምታ መልእክቱ ላይ ችግር የለበትም። አሁንም የማምንበት ነው። የቡርቃ ዝምታን በመፃፌ እንደማልፀፀት ደጋግሜ ተናግሬያለሁ። የኦሮሞ ህዝብ ሰብእና ላይ የተፈፀመውን ግፍ የሚያሳዩ የጥበብ ስራዎች ወደፊትም መፃፍ አለባቸው። መሸፋፈን መፍትሄ አይሆንም። አብሮ ለመኖር ባለፈው ታሪክ ላይ መተማመን ይገባል። የቡርቃ ዝምታ የጭቆናውን ክብደት ለማሳየት የሞከረ መፅሃፍ ነው። የጭቆናውን ክብደት ማወቅ ተከባብሮ ለመኖር ያግዛል እንጅ የዘር ጦርነትን አይቀሰቅስም።     

·         ተስፋዬ ገብረአብ ጠቡ ከኢህአዴግ ጋር ሳይሆን ከኢትዮጵያ ነው የሚሉህ ሰዎች ለዚህ እንደ ማሳያ የሚያቀርቡት መጽሐፍህ   በአማራ በትግሬ እና በኦሮሞ ህዝብ ቁርሾዎች ላይ ብቻ ያተኮሩ በመሆናቸው ነው ይላሉ? ምን ትላለህ? 

Ø  ስለ ዘር መነጋገር ወቅቱ ያመጣው አጀንዳ ነው። በየትኛውም የፖለቲካ ውይይቶች ላይ ቁርሾዎች የመወያያ አጀንዳ ሆነዋል። እኔ የጀመርኩት አይደለም። ክልላዊነትን ያስቀደመ የፖለቲካ ስርአት ነው ያለው። የማንነት ጥያቄ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖአል። አንድ የጥበብ ሰው የዘመኑን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድርጎ መፃፍ ግዴታው ነው። “በአማራና በኦሮሞ መካከል ፀብ ለመፍጠር” የሚል አባባል እሰማለሁ። ይህ አባባል ከቡርቃ ዝምታ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። የቡርቃ ዝምታ ታሪክ የኦሮሞ ህዝብ ስለ ራሱ ከሚያውቀው አንድ አራተኛውን እንኳ አልያዘም። ታሪኩን፣ አባባሎችን ቃላትን ያገኘሁት ከኦሮሞ ገበሬዎች እንጂ ከራሴ ፈጥሬው አይደለም። ያልተለመደ አቀራረብ ስለሆነ ሰዎች ሊሰጉ ይችላሉ። አዲሱ ወጣት ትውልድ መራራ ቢሆንም እንኳ እውነትን የመስማት ችሎታ አዳብሮአል። የሚደርሱኝ ደብዳቤዎች ይህን ጠቁመውኛል። በግልፅ በመነጋገር ችግሩ ይታወቃል። ችግሩ ከታወቀ ነው መፍትሄው የሚገኘው። በማድበስበስና በመሸፋፈን ግጭቶችን ማስቀረት አልተቻለም። ደርግም ሃይለስላሴም ሞክረውት አልተሳካም። ይልቁን ማፈን መፍትሄ እንዳልሆነ ማረጋገጫ ሰጡ። የታመቀ ስሜት ቢፈነዳ ይመረጣል።ቢነገር ይሻላል። ሲተነፍስ መፍትሄውም አብሮ ይመጣል። 

·         ከዚህ በፊት በአንተ ሎግ ላይ ያሰፈርካቸው  የልዑሉ እናትየመነን 4ተኛ ባልእና የንጉሱ ሴት ልጅመጣጥፎች ያነበቡ ሰዎች የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት ለመቀባት ሆን ብለህ ያደረግከው ነው ለሚሉት ምን ትላለህ? 

Ø  በ’ርግጥ የመሪዎች ደካማ ጎኖች ላይ የመፃፍ ፍላጎት አለኝ። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ በጎ እና ጠንካራ ጎናቸው ብቻ ነው ተደጋግሞ የሚፃፈው። መፃህፍት መሪዎችን በማሞገስ የተሞሉ ናቸው። ደካማ ጎናቸው በግልፅ ቢፃፍ አንባቢ ብዙ ትምህርት ያገኛል ብዬ አምናለሁ። በተለይ ደ’ሞ መሪዎች እንደ ማንኛውም ሰው ተራ ሰዎች መሆናቸውን ማሳየት እፈልጋለሁ። በአካባቢያችን መሪዎችን የማምለክ ዝንባሌ አለ። ከወረዳ አስተዳዳሪ ጀምሮ ለተቀመጡ መሪዎች መስገድ ባህል ሆኖአል። መነሻዬ ይህ እንጂ ሌላ አይደለም። እንደ ደራሲ ታሪኩ እውነት እስከሆነ ድረስ በማንኛውም ርስሰ ጉዳይ ላይ እንደፈለግሁ አገላብጬ የመፃፍ መብት አለኝ። ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ልሰራባቸውም እችላለሁ። ያም ሆኖ ተፈሪ መኮንን ለመነን 4ኛ ባሏ የመሆኑ መረጃ ስለ ፖለቲካዊ ጋብቻ ግንዛቤ ይሰጣል እንጂ ንጉሱን አያዋርድም። ደጃዝማች ተፈሪ 4 ልጆች ያላት ወይዘሮ በማግባቱ አደንቀዋለሁ። “ልጃገረድ ካልሆነች አናገባም” ለሚሉ አክራሪዎች ጥሩ አርአያነት ነው። መንግስቱ ሃይለማርያም ውባንቺ ቢሻው የተባለች ሚስቱን ያገባው አስገድዶ በጠለፋ ነው። ከዚህ ምንም ትምህርት አይገኝም።  አዜብ መስፍን ለመለስ ዜናዊ ሻይ እንድታፈላ በድርጅቱ የተመደበችለት ታጋይ ነበረች። በዚያው ጠቀለላት። ይሄ ጥሩ ነው። እንዲህ ያሉ ታሪኮችን የመፃፍ ፍላጎት አለኝ። እንዳልኩት በመሪዎች ትከሻ ላይ የተቆለለውን የመኮፈስ ካባ ገፍፌ መጣል እፈልጋለሁ። “የልዑሉ እናት” የሚለውን ታሪክ የፃፍኩት የጳውሎስ ኞኞን መፅሃፍ መሰረት አድርጌ ነው። “የመነን 4ኛ ባል” ዘውዴ ረታ ከፃፉት የተወሰደ ነው። እኔ ስፅፈው የተለየ የሚሆንበት ምክንያት ምንድነው? እንዲህ የሚያስቡ ሰዎች ልባቸው ውስጥ የሸሸጉትን የዘረኛነት በሽታ ያክሙት ዘንድ እመክራቸዋለሁ። ሰዎች ስለኔ የሚያስቡትን ግምት ውስጥ እያስገባሁ ልፅፍ አልችልም። በማንኛውም ርእሰ ጉዳይ ላይ በራሴው እይታ እንዳሻኝ እፅፋለሁ። አንባቢዎቼን ለማስደሰት ወይም ለማናደድ ብዬ አይደለም የምፅፈው። ቢታተምም ባይታተምም የኔ ችግር አይደለም። ኳስ መጫወት የሚወዱ ሰዎች ኳስ ይጫወታሉ። እኔም መፃፍ ስለምወድ እፅፋለሁ። ሽማግሌው ቱርጌኔቭ እንደሚለው በጎ ከሰራን፣ ስራችንም ዋጋ ካለው፣ ያን ዋጋ ህዝብ ማስተዋል ከቻለ ለስራችን ክብር ይሰጠናል።   

·         በብዙ ጽሁፎችህ ለኦሮሞ  መብት ጥብቅና የመቆም  ዝንባሌ ታሳያለህ፡፡ ነጋሶ እንዳሉት ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ነኝ ማለትን ታበዛለህ ለሚባለው ምላሽህ ምንድን ነው?

Ø  የነጋሶን አባባል ሰምቼዋለሁ። More catholic than the Pope የሚለውን አባባል ገልብጠው ሊጠቀሙበት ነው የሞከሩት። ነጋሶ ጭንቅላታቸውን ተናግረው አያውቁም። ሌሎችን ለማስደሰት በማሰብ የመናገር ልማድ አዳብረዋል። ነጋሶ አሁን የአንድነት ሊቀመንበር ናቸው። አራተኛ ድርጅታቸው መሆኑ ነው። ከኦነግ ወደ ወያኔ፣ ከወያኔ ወደ አንድነት ሲዘሉ ምንም አልተደናቀፉም። መርህ ያለው ሰው እንዲህ በቀላሉ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ መዝለል አይቻለውም። ጨለንቆ ላይ ጉድጓድ አስቆፍረው አፅም እየሰበሰቡ “ነፍጠኛውን” ያወግዙ እንዳልነበር፣ አኖሌ ላይ ስለ “ጡት መቆረጥ” ታሪክ ሲያስተምሩ እንዳልነበር አሁን 180 ዲግሪ ተገልብጠው የራስ ጎበና ዳጪ ተከታይ ሆነዋል። እድሜ ከሰጣቸው የነገውን አናውቅም። በተቀረ ለኦሮሞ ህዝብ ጥብቅና መቆም ሃጢአት አይደለም። ሃጢአት ሊሆን የሚችለው ከተገፋና ካመፀ ህዝብ ጎን አለመቆም ነው። ለኦሮሞ ህዝብ መቆም ሲባል ሌላውን ህዝብ ማጥቃት ማለት አይደለም። ጥያቄው የክብርና የእውቅና ማግኘት ጥያቄ ነው። የኦሮሞን የሞጋሳ ባህል የሚያውቅ በነጋሶ አባባል በጣም ይገረማል። ያም ሆኖ እኔ በኦሮሞ ህዝብ መካከል ተወልጄ ያደግሁ፤ ራሴን ኦሮሞ ብዬ ለመጥራት የሞራል ብቃት ያለኝ ሰው ነኝ። ልጅ እያለን የኢብሳ ኦሮሞ የጠበል ጠላ ስንቀምስ፣ Ijollee warra Bishoftu ነበር ፉከራችን! በእነዚያ የልጅነት ዘመናት ጋራቦሩ ላይ እርጎ ጠጥተን ስናበቃ ከአህያ እስከ ፈረስ እየጋለብን ነው ያደግነው። ይህ ፖለቲካ አይደለም። ህይወት ነው። ማንነት የተገነባበት ንጥረነገር ነው።    

·         በጹህፎቸህ ውስጥ  የበቀል ስሜት የለህም ወይ? ጹህፎችህ  የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ የሚያደርግ ገንቢ ሃሳብ ምንም ቦታ ላይ የለም ትባላለህ። ለምን? 

Ø  በግልባጩ የኔ ፅሁፎች ለአንድነት የቆሙ ናቸው። ችግሮችን በግልፅ አውጥቶ መፃፍ ለመፍትሄ ፈላጊዎች ግማሹን ስራ እንደሰራሁላቸው ነው የሚቆጠረው። በቀል የሚለው ቃል እኔን አይገልፀኝም። በግል የበደለኝ ሰው ወይም ህዝብ የለም። ለበቀል የሚያበቃ የማስታውሰው ጉዳት አልደረሰብኝም። በቀል ቀርቶ በጥላቻ የማስታውሰው ሰው እንኳ የለም። በቀል የሚኖረው ቂምና ጥላቻ ሲኖር ነው። በኔ ልብ ውስጥ ለቂምና ለጥላቻ ቦታ የለም… 

·         ከኢትዮጵያና ኤርትራ ስሜትህ ለየትኛው ቅርብ ነው? 

Ø  ኢትዮጵያ የትውልድ አገሬ ናት። በደም ኤርትራዊ ነኝ። ማንነት የብዙ ግብአቶች ውጤት እንደመሆኑ ለሁለቱም አገራት ስሜት አለኝ። ቋንቋ፣ ባህል፣ አስተዳደግ፣ ወላጆች እነዚህ ሁሉ ማንነትን የሚገነቡ ግብአቶች ናቸው። ጥያቄው ስለ ዜግነት ከሆነ ሆላንድ የዜግነት አገሬ ሆናለች። በቀሪው የህይወት ዘመን በዚሁ የዜግነት ሰነድ መንቀሳቀስ እችላለሁ። 

·         ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደፊት የመዋሃድ ዕድል ይኖራቸው ይሆን?

Ø  ተመልሰው የሚዋሃዱ ቢሆኑ ኖሮ 30 አመት ትግል አይደረግም ነበር። በሰላሳ አመታቱ ጦርነት ከሁለቱም ወገን በአስር ሺዎች ተሰውተዋል። እንደገና በድንበር ጦርነት በተመሳሳይ የብዙ ሺዎች ህይወት ተቀጥፎአል። ከዚህ ሁሉ በሁዋላ ስለ አንድነትና ውህደት መነጋገር የሚቻል አይመስለኝም። ከመነሻውም የኤርትራ ጥያቄ የነፃነት ጥያቄ ነበር። ስለዚህ ሁለቱ አገራት ተከባብረው እንደ ጎረቤት በሰላም መኖር ከቻሉ እንኳ ትልቅ ድል ነው። እንደ አውሮፓውያን ድንበራቸውን አፍርሰው፣ የንግድ ህግ ደንግገው በሰላም መኖር ከቻሉ ትልቅ ስኬት ይሆናል። ሁለቱ አገራት የየራሳቸው ፀጋ አላቸው። ከመዋሃድ ባላነሰ ተግባራዊ ሊሆን በሚችል መልኩ በትብብር መስራት ይችላሉ። ኤርትራና ኢትዮጵያን በተመለከተ የኔ ምኞትና ፍላጎት በአዲሱ መፅሃፌ ላይ በግልፅ ተቀምጦአል። በአፍሪቃ ቀንድ ደረጃ በጋራ ለመስራት ከወዲሁ ጥርጊያ መንገዱን ቢያነጥፉ የአካባቢው 140 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል። የአፍሪቃ ቀንድ ህዝቦች ከጦርነት የሚገኘውን ኪሳራ ከማንም በላይ ይገነዘቡታል። ስለዚህ ሰላማዊ አካባቢ ለመፍጠር በቁርጠኛነት መተባበር ብቻ ነው የሚያዋጣቸው።   

·         “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የተባለው መጽሐፍህ ግነት እንደነበረበት ተናግረህ ነበር። አሁኖቹ መጽሃፍት በሆነ ወቅትግነት ነበራቸው’ ላለማለትህ ምን ዋስትና አለ? ለሚሉ አስተያቶች ምላሽህ ምንድነው? 

Ø  “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” በነፃነት የተሰራ ስራ አልነበረም። መፅሃፉ የኔው ፕሮጀክት ቢሆንም በመካከሉ ድርጅታዊ ጣልቃ ገብነት መጣ። ሁዋላ ከፕሮጀክቱ ራሴን ያገለልኩት በትእዛዝ መፃፍ ስላልፈለግሁ ነው። በግሌ በሰራሁዋቸው ስራዎች ላይ ስለ ግነትም ሆነ ስለ መፀፀት ተናግሬ አላውቅም። 

·         እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከመፃፍህ አንጻር ስለ ኤርትራ ምንም አለመጻፍህ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው። ለምን? 

Ø  ገና ፅፌ መቼ አበቃሁ? የመሞቻዬ ጊዜም ገና አልደረሰም። የ45 አመት ሰው ነኝ። የመፃፊያ ጊዜዬ ገና መጀመሩ ነው። እነዚህ ማስታወሻዎች ወደ ስነፅሁፍ ስራ ለመግባት እንደመንደርደሪያ የተጠቀምኩባቸው ብቻ ናቸው። ከእንግዲህ ቢያንስ በየአመቱ አንድ መፅሃፍ ለማሳተም እቅድ አለኝ። በፕሮግራሜ መሰረት መቼ፣ ስለማን፣ ምን መፃፍ እንዳለብኝ መወሰን ያለብኝ እኔ ነኝ። ከዚህ ቀደም፣ “ስለ እዚህ ጉዳይ ለምን አልፃፍክም?” ተብሎ የተጠየቀ ደራሲ ያለ አይመስለኝም። ስለፃፍኩት እንጂ ስላልፃፍኩት ጉዳይ ልንነጋገር አይገባም። የሚገርመው “ለምን አልፃፍክም?” ተብዬ የምወቀሰው ስለማላውቀው ጉዳይ ነው። የምሰራው መፅሃፍ እንጂ ዜና አይደለም። በርግጥ ይህን ክስ የሚያራግቡት ወያኔዎች መሆናቸውን አውቃለሁ። ያቀረብኩትን መረጃ ማስተባበል ስላልቻሉ በዚህ ፕሮፓጋንዳ ከአንባቢ ሊነጥሉኝ ይሞክራሉ። ያም ሆኖ ባለፉት አመታት ወደ ኤርትራ የተጓዝኩ እንደመሆኑ የኤርትራ ጉዞዬን በአዲሱ መፅሃፌ ተርኬዋለሁ። ጀምሬያለሁ። እቀጥላለሁ… 

·         መለስ ራዕይ ነበራቸው  በሚባለው ጉዳይ ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው። አንተስ? በቅርቡ በታተመ መጣጥፍህ፣መለስ ተመልሰው ቢመጡ አባይ ፀሐዬን እስር ቤት ያስገባው ነበር” ያልክበት ምክንያት ምንድነው 

Ø  የመለስ ራእይ የሚባለውን የፕሮፓጋንዳ መፈክር መለስ ሲሞት በተደናበረ ሁኔታ የፈጠሩት ነው። መለስ ሲሞት እንደ ኢህአዴግ ማእከል ሆኖ ሊያሰባስባቸው የሚችል አይዲዮሎጂ አልነበራቸውም። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ ማንም ሳያውቀው አርጅቶ ሞቶ ነበርና አደጋ ላይ ወደቁ። “ምንድነው የመለስ ራእይ?” ብለህ ብትጠይቅ አንዳንዱ የዋህ ካድሬ፣ “የአባይ ግድብ”፣ “የባቡር ፕሮጀክት” ምናምን ይልሃል። የአባይ ግድብ ጥናት በጃንሆይ ዘመን የተጠና ነው። አቅም እና ምቹ ጊዜ እየተጠበቀ ነበር። ግብፅ ስትዳከም ምቹ ጊዜ ሆኖ ተገኘ። የባቡሩ ፕሮጅክት የሃይሉ ሻውል እቅድ ነው። ቅንጅት በ2005 ምርጫ ስልጣኑን ቢይዝ ሊፈፅመው ያቀደው ነው። ወያኔ ከአፍ እየቀለበ የመንጠቅ ልዩ ችሎታ አለው። “የመለስ ራእይ” የሚባል ነገር የለም።  አሁን እንኳ ሽኩቻ ውስጥ ስለገቡ የራእዩ ከበሮ ረገብ ብሎአል።  በመለስ ራእይ ስም መለስ የዘረጋውን መዋቅር በመበጣጠስ ላይ የሚገኘው አባይ ፀሃዬ ነው። አንዱ ጠንክሮ እስኪወጣ ድረስ ሽኩቻቸው ይቀጥላል።  

በመለስ ራእይ ስም መለስ የዘረጋውን መዋቅር በመጣጠስ ላይ የሚገኘው ዓባይ ፀሃዬ ነው ያልክበት ምክንያት ምንድነው? 

Ø  የሽኩቻው ድራማ ዋና አክተር አባይ ፀሃዬ ነው። በአፋቸውየመለስ ራእይይላሉ። በተጨባጭ ግን የመለስ ታማኞችን እየመነጠሩ ነው። መለስ ይዞት የነበረውን ብቸኛ አምባገነናዊ ሃይል ለመቆጣጠር እየሰራ ነው። ርግጥ ነው፣ አባይ ፀሃዬ በሚፈፅመው ድርጊት ተቃውሞ የለኝም። ለአገር ደህንነት ሲል አለመሆኑ ግን መታወቅ አለበት። አጤ ምኒልክ ሲሞቱ በደጃዝማች ተፈሪ እና በልጅ ኢያሱ መካከል የተፈጠረውን የስልጣን ሽኩቻ የሚያስታውስ ሁኔታ ላይ ነን። አባይ ወልዱ እንደ ወራሽ ልጅ እያሱ - አባይ ፀሃዬ እንደ ደጃዝማች ተፈሪ! በትክክል ተመሳሳይ የታሪክ ጊዜ ላይ ነን።   

·         እንደምታውቀው ኢሕአዴጎች “እዚህ ያለነው የመለስን ራዕይ ከግብ ለማድረስ ነው” ብለው ውሳኔ ላይ ደርሰው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዓመት አልፏቸዋል:: አንተ ደግሞ  “የመለስ ራእይ” የሚባል ነገር የለም ብለሃልና ብታብራራው? 

Ø  መለስ ለመሞት አንድ ሳምንት ሲቀረው ነው ባለራእይ የሆነው? ምንድነው የሚያወሩት እነኚ ሰዎች? 20 አመታት ከመለስ አመራር የተገኘው ምንነበር? በዘር ከፋፍለው ህዝቡ እንዳይተማመን አደረጉት። ያልነበረበትን የሃይማኖት ግጭት ስር እንዲተክል ጥረት አደረጉ። በሰላም አስከባሪ ስም የዜጎችን ህይወት ቸበቸቡ። የምርጫ ኮሮጆ በመገልበጥ ህዝቡ በዴሞክራሲ ላይ ያለውን እምነት አሳጡት። ምንድነው የመለስ ራእይ የሚባለው ቀልድ? ጄኔራሎችን ከህወሃት ብቻ መሾም ራእይ ነው? ቡና ሲወቀጥ ግድግዳቸው የሚሰነጠቅ የኮንደሚንየም ቤቶችን መገንባት ራእይ ነው? ገበሬዎችን አፈናቅለህ ስታበቃ አንድ ሄክታር መሬት በአንድ ፓኮ ስጋራ ዋጋ መቸብቸብ ራእይ ነው? አንድ ፍሬ እህቶቻችንን ለአረብ ግርድና አሳልፎ መስጠት ነው ራእይ? በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙ፣ ኦልባና ሌሊሳ ለምን ታሰሩ? በመከላከያ ስም ሸቀጥ ያለቀረጥ በማስገባት የአገር ውስጥ ነጋዴዎችን መግደል ራእይ ነው? ምንድነው የመለስ ራእይ? ውሸትን በመደጋገም እውነት የማስመሰልን ጥበብ ተክነውበታል። 

·         በዚህ ወቅት ሕወኃት ለሁለት ተከፍሏል በሚባለው ትስማማለህ? ከሆነስ እነማን በአሸናፊነት የሚወጡ ይመስልሃል?  

Ø  በሁለቱ አባዮች (አባይ ፀሃዬ እና አባይ ወልዱ) መካከል ጦርነት መኖሩን እየሰማን ነው። መረጃው ግን የተረጋገጠ ነው ለማለት አልደፍርም።  የምንሰማው እውነት ከሆነ ከመቀሌው አባይ በስተጀርባ ቴዎድሮስ ሃጎስ አለ። ከአዲሳባው አባይ ስር እነ ጌታቸው አሰፋ፣ እነ ደብረፅዮን መሰለፋቸው ይሰማል። ሳሞራ የአዲሳባውን አባይ ተቀላቅሎአል። አዜብ ‘አርፈሽ ቁጭ በይ! የመለስን ፋውንዴሽን ተከታተይ’ ተብላለች። እብድ ስለሆነች ያልተጠበቀ ነገር እንዳትፈፅም በመስጋት ሰንሰለቷን ሁሉ በጣጥሰውባታል። የዘረፋ ቀዳዳዎቿን እየዘጉባት ነው። ያም ሆኖ አዜብ አርፋ ትቀመጣለች ተብሎ አይታመንም። መሞከሯ አይቀርም። የግል አስተያየቴን ለመስጠት ያህል፣ የመቀሌ - አዲሳባ ሽኩቻ ይፋ ሳይወጣ ውስጥ ውስጡን ሊጠናቀቅ ይችላል። ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ሽጉጥ ከተኮሱ ቤተመንግስቷን ለዘልአለሙ እንደሚያጧት ያውቃሉና ሽጉጥ ወደ መምዘዝ የሚገቡ አይመስለኝም። ከሁለቱ ቡድኖች አንደኛው እስኪያሸንፍ ሃይለማርያም ወንበሩን በታማኝነት ይጠብቅላቸዋል። ማን በአሸናፊነት ሊወጣ እንደሚችል አብረን እናየዋለን። የአዲሳባው ቡድን የሚበረታ ይመስለኛል። ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከሁለቱም ቡድኖች ገለልተኛ ሆኖ የአስታራቂነት ሚና ለመጫወት እሞከረ ነው። ምናልባት እሱን በማንገስ ልዩነታቸውን ይፈቱ ይሆናል።    

·         ሕወኃት በምርጫ  ስልጣን የሚለቅ ይመስልሃል?  

Ø  በግልፅ ተናግረዋል። “ጀርባችንን በእሳት ሰንሰለት እያስገረፍን ያገኘነውን ወንበር በምርጫ ካርድ ስም ሳምሶናይት ይዘው ለመጡ ሰዎች አናስረክብም” ብለዋል። በርግጥ የምኒልክን ወንበር በምርጫ አላገኙትም። ስለዚህ በምርጫ መልቀቅ አይፈልጉም። በምርጫ እንደማይለቁትም በ2005 ምርጫ አስመስክረዋል። በተመሳሳይ በ2010 ማንኛውንም አይነት የማጭበርበር ዘዴ በሙሉ ሃይላቸው ስለተጠቀሙበት 99.6 በመቶ በማሸነፍ ወንበሮቹን ሁሉ ያዙ። በምርጫ በኩል ይገኛል የተባለውን የዴሞክራሲ ጭላንጭልም ደፈኑት። ከዚህ በሁዋላ ምንድነው የሚጠበቀው? 

·         የሕወኃት በኃይል ስልጣን ላይ የመቆየት አባዜ የሚያዛልቅ ይመስልሃል  

Ø  አዛልቆአቸው 22 አመት ሆኖአቸዋል። ሌላ 22 አመታት እንደማይገዙ ምንም ዋስትና የለም። ወያኔና ሻእቢያ በጠመንጃ ባይመጡበት ደርግ እስከዛሬ ስልጣን ላይ ሊቆይ ይችል ነበር። ሙጋቤ አሁንም አለ። ጋዳፊ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ነበረ። ስዩም መስፍን ቻይና የሚማሩትን የህወሃት የአመራር አባላት ልጆች እያሰለጠነ ነው። በቻይና መንግስት ድጋፍ ተተኪ የአገሪቱ መሪዎች ሊያደርጓቸው ይፈልጋሉ። ይህ ተረት አይደለም። እስከቻሉት ድረስ ይሞክራሉ። ከአንዳንዶቹ ጋር እንዲህ በስልክ ስናወራ “ከዚህ በሁዋላ 40 አመታት መቆየት እንችላለን” ብለው በቀልድ መልክ ጣል ያደርጋሉ። እየቀለዱ ግን አይደለም። “የ65ሺህ ጓዶቻችንን ህይወት የከፈልነው ዋጋው ውድ ነው” ይላሉ። በጨዋታ መሃል ከምኒልክ እስከ ሃይለስላሴ የነበረውን ዘመን ያሰሉታል። የንጉስ ሳህለስላሴ የልጅ ልጆች የቤተሰብ ጥል እየተጣሉም ቢሆን ስልጣን ከቤተሰባቸው ሳይወጣ እየተተካኩ ቆይተዋል። ህወሃት በተመሳሳይ መንገድ ልዩነት የፈጠሩትን እያስወገደ ሁለት ወይም ሶስት ትውልድ ከዚያም በላይ ለመግዛት ይችላል አይነት ወጎች አሏቸው። በአደባባይ ደግሞ፣ “እኛ በስልጣን መቀጠል ካልቻልን ኢትዮጵያ ትበታተናለች” ብለው መዛታቸውን ቀጥለዋል። ኢትዮጵያ እንዳትበታተን በመስጋት ህዝቡ ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛላቸው ይመኛሉ። 

·         ሕወኃትን 22 ዓመታት በስልጣን እንዲቆይ ያስቻለው ምንድነው ትላለህ? 

Ø  ምስጢሩ ህዝቡን ከፋፍሎ መግዛት በመቻሉ ነው። የፌደራል አገዛዝ ስርአቱን ለስልጣን ማራዘሚያ ተጠቅሞበታል። ክርስትያኑን በሙስሊሙ ያስፈራራዋል። የአማራው ሃይል ሲበረታ በኦሮሞው እየመታ ዘልቆአል። ሌላ ምስጢር የለውም። ከፋፍሎ በመግዛት፣ የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜትን በማዳከም፣ ከተቻለ ጨርሶ በማጥፋት ዝንተ አለም መግዛት እንደሚችሉ አስልተው ጨርሰዋል። በርግጥ 95 በመቶ የመከላከያን አመራር ተቆጣጥረውታል። ደህንነቱ ሙሉ በሙሉ በእጃቸው ነው። ህዝቡ በዘር ተከፋፍሎአል። ለሃያላኑ አገራት ራሳቸውን በአገልጋይነት ስላቀረቡ በጫና ፈንታ እርዳታ እያገኙ ነው። የዚህ ሁሉ ድምር በስልጣን እንዲቆዩ አግዞአቸዋል። 

·         አሁን ያሉት ብዙዎቹ የሕወኃት ባለስልጣናት በአባት ወይም በእናት ኤርትራውያን ናቸው ይባላል:: የተባለው ትክክል ከሆነ ውሳኔዎቻቸው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ሊሆን አይችልም? ከዚሁ ጋር ተያይዞ የእነኚሁ ባለስልጣናት አያቶች  ወይም ቅድመ አያቶች የጣሊያን ባለሟሎች የነበሩ ናቸው ስለሚባለው ምን መረጃ አለህ? የባንዳ ልጆች መሆናቸው የስነ ልቦና  ቀውስ ውስጥ አይከታቸውም ? 

Ø  በአባት ወይም በእናት ኤርትራዊ መሆን የዘመናችን ዋና አጀንዳ መሆኑ ያሳዝነኛል። በረከት ስምኦን በእናቱም ሆነ በአባቱ ኤርትራዊ ነው። ለኤርትራ የፈፀመላት በጎ ነገር አለመኖሩን ግን አረጋግጥልሃለሁ። በረከት በኤርትራውያን ዘንድ በጣም የተናቀ ሰው ነው። እንደ ፖለቲከኛ እንኳ አያዩትም። በኢትዮጵያውያንም አይታመንም። እድለኛ አይደለም። ይህ ሊሆን የቻለው በረከት የሚሰራው ለግሉ፣ ለዝናው፣ ለስልጣን ስለሆነ ነው። ግማሽ የኤርትራ ደም ያላቸው የህወሃት አመራር አባላት ለኤርትራ ያደላሉ ብዬ አስቤ አላውቅም። የተወለዱት እና ያደጉት ትግራይ ነው። ለትግራይ ነው የሚሰሩት። አንድን ሰውግማሽ ኤርትራዊ ነውብለን ከማሰባችን በፊትግማሽ ኢትዮጵያዊ ነውየሚለውን ማስቀደም ለምን አልተቻለም? በአሉ ግርማ እኮ በአባቱ ህንዳዊ ነው። ገብሩ አስራት ግማሽ ጎጃሜ ነው። ጆሴፍ ስታሊን ሩስያዊ አልነበረም። ኦባማ በአባቱ ኬንያዊ ነው። ጥላሁን ግዛው የፊውዳል ቤተሰብ ነበር።ለኢትዮጵያዊነት ህይወታቸውን የከፈሉ ኤርትራውያንን ስም እንጥራ ብንል ሰአታት አይበቃንም። መለስ በአባቱ ኢትዮጵያዊ ነው። ለምንድነው ወደ እናቱ ጎሳ ያዘነብላል ተብሎ የሚታሰበው? ተወልዶ ያደገው ትግራይ ነው። መለስ ኢትዮጵያን ለመምራት ግማሽ ኢትዮጵያዊነቱ ከበቂ በላይ ነበር። እንደሚመስለኝ ችግሩ ግማሽ ኤርትራውያን መሆናቸው ሳይሆን መርህ አልባ፣ ወይም ስልጣናቸውን ብቻ የሚያስቀድሙ በመሆናቸው ሊሆን ይችላል። መለስ ዜናዊ የባንዳ ልጅ ስለመሆኑ ሲነገር የሰማሁት ከገብረመድህን አርአያ ነው። ገብረመድህን ስለሚያጋንን አይመቸኝም። የሆነው ሆኖ መለስ የባንዳ ልጅ ሊሆን ይችላል። የባንዳ ልጅ መሆኑ ግን እሱንም ባንዳ አያደርገውም። የመለስን ወላጆች እና ልጆች እንተዋቸው። መለስን ለመውቀስ የሚያበቃ በአገር ላይ የፈፀመው በርካታ ወንጀል አለ።

·         መለስ ዜናዊየኤርትራ ህዝብ ከየት ወዴትየሚለውን መጽሐፍ መጻፋቸው፣ ኤርትራ ራስዋን ችላ ነፃ ሐገር ሆና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና እንድታገኝ ለዋና ጸሐፊው ቡትሮስ ጋሊ ደብዳቤ  መጻፋቸው፣ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ ይገባኛል እንዳትል እንቅፋት መፍጠራቸውና ለኤርትራ ይገባል ማለታቸው ግማሽ  ኤርትራዊ ባይሆኑ ኖሮ የሚሞክሩት ተግባር ነበር 

Ø  ኤርትራን በተመለከተ በተወሰኑ ውሳኔዎች የኤርትራ ደም የሌለባቸውም ተሳትፈው አብረው ወስነዋል። የፖለቲካ አቋማቸውን ነው ያስፈፀሙት። ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር ስለመቀጠሏ እንኳ ሁለት ልብ ስለነበሩ የኤርትራን ነፃነት የማይቀበሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም። ከዚያም ባሻገር አቋማቸውን ለመለወጥ ቢያስቡ ኖሮ እንኳ በወቅቱ ምንም ማድረግ አይችሉም ነበር። ተዋጊ የገበሬ ሰራዊትና ፖለቲካ የሚያንበለብሉ ሸምዳጅ ካድሬዎች እንጂ ሌላ አቅም አልነበራቸውም። አዲሳባን እንዴት እንደሚያስተዳድሩ አሳቡ እንኳ አልነበራቸውም። በርግጥ መለስ ዜናዊ ኤርትራን በተመለከተ ስሜቱ ስስ መሆኑ ብዙ የተባለበት ነው። ስለ መለስ የልብ ሚዛን የሚያውቀው ራሱ መለስ ብቻ ነበር። ሳይፅፈው ተሰናብቶአል።   

·         መለስና ጓደኞቻቸው  ሽንጣቸውን ገትረው ለኤርትራ ነፃነት ሲዋጉ የነበሩት  ለምን ይመስልሃል? 

Ø  እኔ እስከማውቀው ለኤርትራ ነፃነት የተዋጉት ኤርትራውያን ናቸው። መለስና ጓደኞቹ የራሳቸው አጀንዳና አላማ ነበራቸው። በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት ለስልጠና ኤርትራ ሄደው መስዋእትነት እንደገጠማቸው ሰምቻለሁ። የሻእቢያ ተዋጊዎችም በተመሳሳይ ህወሃትን በማገዝ ሂደት ውጊያ ላይ መስዋእትነትን ከፍለዋል። ይህ የጋራ ጠላትን ለመመከት ከተደረገ ታክቲካዊ ትብብር ያለፈ ስም ሊሰጠው አይችልም። የህወሃት እገዛ አንዳንድ ፀሃፊዎች አጋንነው እንደሚያቀርቡት አይመስለኝም።  

·         በኢትዮጵያ ባለጠመንጃ አስተዳዳሪ መሆኑ የሚቀርበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልሃል? 

Ø  ተስፋ አደርጋለሁ። 

·         የሕወኃትን በኃይል ከስልጣኑ እናባርረዋለን የሚሉት ተቃዋሚዎች ሚሳካላቸው ይመስልሃል 

Ø  ህዝቡ የወያኔን ስርአት ተንኮል ጠንቅቆ ተረድቶ አማፅያኑን በሙሉ አይኑ ማየትና ማመን ከጀመረ የሚሳካላቸው ይመስለኛል። በርግጥ እኔ በግሌ ጠመንጃ እንዲተኮስ አልፈልግም። ወጣቶች በጦርነት እንዲሞቱ አልመኝም። እኔ ራሴ የጦርነት ትራፊ በመሆኔ ህመሙ ይሰማኛል። ጠመንጃ ከማንሳት ባሻገር አማራጭ መጥፋቱ ግን ያሳዝነኛል።

 


No comments: